Wednesday, August 25, 2021

ማርያም ማለት ገነት መርታ የምታገባ ማለት ነዉ

     
  ፍልሰታ ለማርያም !

 ሕጻናት በፍቅር የሚጾሟት እነ ቀዉስጦስ መልአክ እና አባ ሳሙኤል ዘደብረ ቀልሞን በምስራቅ በኩል ለሚቆሙ ለሚያስቀድሱ በቤተልሔም አካባቢ በረድኤት የሚገለጹበት ሱባዔ፤ እመቤታችን ድንግል ማርያም ከቅዱስ ሚካኤል እና ከቅዱስ ገብርኤል ጋር በይበልጥ ኢትዮጵያን እና ሕዝቦቿን ተገልጣ የምትባርክበት ሳምንታት፤

አንቲ ዉእቱ ማዕጠንት ዘወርቅ እንተ ጾርኪ ፍሕመ እሳት ቡሩክ ቡሩክ እሳት የተባለ ልጇ እንዴት ያለ እሳት ነዉ ቡሩክ የሆነ እሳት እያልን የቅዳሴ ተሰጥኦ የምንቀበልበት የሚናፈቅ ጊዜ፤

መክፈልት ዳቦ እንጀራ ቋጥረን ደጄሰላሙ ላይ አስቀምጠን ሠራዊተ መላእክቲሁ ለመድኃኔዓለም ሲባል ቁርባናችን እንደደረሰ አዉቀን በየጾታችን ተሰልፈን ቆርበን ወደ አስቀመጣናት ምግብ ስንሮጥ አንዳንዴ እርስ በእርስ መሰራረቁም ነበር፤

ታዲያ መላእክት አብረዉን አስቀድሰዉ ሕጻናት በመሆናችን ቂም በቀል ስለሌለን ከእኛ ጋር መቆየታቸዉ ደስ ቢያሰኛቸዉም ቅዳሴዉ ሲጠናቀቅ ጸሎቱን፤ ቁመቱን መስዋዕቱን ማሳረግ ስላለባቸዉ ከሁለት ሰዓታት በኋላ ይለዩናል፤

አሁንማ ታላላቆች ሁነናል ቆመን ማስቀደስ ብንችልም ቂም ይዘን ተጣልተናል ንስሐ ሳንገባ ጾሙ ገብቷል፤ እስከማታ ብንጾምም እንደ ሕጻናት ስላልሆንን መላእክት ርቀዉናል፤

ቂም ይዘን ተጣልተን ሰዉ አስቀይመን፤ ሰርቀን፤ ባዕድ አምልከን ዘሙተን፤ ሁለቱን ሱባዔ (ሳምንት) ጥሬ እየቆረጠምን ከምንጾም እንደ ሕጻናት ሁነን አንድ ቀን ብንጾም ሳይሻል አይቀርም፡፡

ለግብጻዉያን በግንቦት ወር በደብረ ምጥማቅ እንደምትገለጸዉ ነሐሴ ወር በተለይ ለኢትዮጵያዉያን ነጭ ሰበኗን ለብሳ ቅዱስ ሚካኤል በቀኝ ቅዱስ ገብርኤል በግራ ሁነዉ የምትገለጽበት መሆኑ የታወቀ የተረዳ ነዉ፤

በዓለም ባሉ በኦርቶዶክሳዉያን አብያተ ክርስቲያናት የሚቆመዉ ቁመት የሚታጠነዉ ማዕጠንት፤ የሚሰዋዉ መስዋእት የሚያርገዉ በአክሱም ጽዮን (ለዓለም በተሰጠችዉ በሙሴ ጽላት) አማካኝነት ነዉ ብንልም ማንም አይሰማንም፤ ኢትዮጵያ የምስጢር ሃገር ናትና ሰላም እንዳታገኝ ከንቱዉ ዲያብሎስ ከፈጣሪ አየቀረበ እባክህ ተወኝ ልፈትናት ይላል፤ ንግስናዉን በመሳሪያ እና በወታደር ካስቀየረ እና ንጉሱን ካስገደለ ጳጳሱን ካሰቀለ በኋላ ደም እያስፈሰሰ እሱን እየላሰ ይኖራል፤

ሱባዔዉን ኃይለ መስቴማን የሚያደክም ሱባዔ ያድርግልን ክፉ ትዉልድ ባያምንበትም አስራት ትሁንሽ የተባለችዉን ሃገራችንን እመቤታችን በጸሎቷ ለሷ ባለን ፍቅር እና ክብር ተመልክታ ዲያብሎስን ታሳፍርልን፤ በደመ ነፍስ የሚገዳደሉትን ቤተሰቦች ታስታርቅልን፤ ያለ ጽዮን እርቅ የለም፤ እድሉ ከተገኜ በጽዮን በደጇ በአበዉ ደናግል መነኮሳት እና ቀሳዉስት ሁለቱም አሽከሮች ይታረቃሉ፤ እምቢ ካሉ ሠይፍ ይበላቸዋል፤ ስዉሩ ነአኩቶ ለአብ ይገለጣል፤ ብረት አንጋቢዎችን ብረቱ ላይ ያሉትን መስተቃትላን አጋንንትን አስወግዶ አስተዋይ ልቦና ይመጽዉትልን፤ አሜን + + +

No comments:

Post a Comment