Thursday, June 25, 2020

አስራት በኩራት !


ሰላም ለኩልክሙ!
ቅዳሜ ግንቦት 15 ቀን 2012 ዓ.ም
ዛሬ ስለ አስራት በጥቂቱ እንማማር ፤
አስራት በጥቂቱ ሰጥተን በብዙ የምንወስድበት ብልጣብልጥነት ነዉ !
የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ፤ የቄሳርን ለቄሳር ስጡ !
ፈጣሪያችን ሁሉ የመላለት ሲሆን ከእርሱ የሆነዉን የእኛን ጥቂት ነገር ለትዝብት እንድንሰጠዉ ይጠይቀናል፤ ሆኖም ግን እኛ መች በዋዛ እሽ አልነዉ ፤ የሚገርመዉ ደግሞ ስጡኝ ያለዉ ለካ ሊያበረክትልን ነበር ፤ ይኽን ጉዳይ ከኋላችን ሁሌም የሚያደባዉ ጠላት ስለሚያዉቅ ከኪስ፤ከባንክ፤ከመሃረብ፤ከመቀነት፤ከካዝና ያለዉን ገንዘባችንን በተጠንቀቅ ይጠብቃል፤ በጸሎት ኃይል አድክመዉ አፍዘዉ ያችን ጥቂት ገንዘብ በፈጣሪ ፊት ሆጭ ሲያደርጉ ከፈዘዘበት ይነቃል ፤ ታዲያ በረከቱ ተመልሶ ሲመጣና ቤቱ ሞልቶ አላልቅ ሲል ይበሳጫል፤ 
ሀቡ ዘቄሣር ለቄሣር ወዘ እግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ፤ (ማቴ 22 ፡ 21) ይኽ ቃል የፈጣሪያችን የክርስቶስ ትዕዛዝ ነዉ ፤ የአብም የመንፈስቅዱስም ትዕዛዝ መሆኑ እንዳይዘነጋ፤ የቄሣርን ደሞዝህ ተቆርጦ ይሰጥሃል፤ በእርሻህ በንግድህ ግብር ትገብራለህ ፤ የእግዚአብሔርን ከመቶ አስር ግን በመንፈስ ቢቆረጥብህም ኪስህ ወይም ባንክ ሒሳብህ ላይ ያለ ስለሚመስልህ ያልሰጠህ ፡ የደበቅኽ ፡የተጠቀምኽ ይመስልሃል፤ ነገር ግን አላየኸዉም እንጂ ተወስዷል፤ በፈቃዳችን ወስደን እንድንሰጥ ያስፈልጋል!
1500( አንድ ሺህ አምስት መቶ) ብር የተጣራ ደሞዝ ያለዉ (ትርፍ ያተረፈ ) ከመቶ አስር 150 ብር የእግዚአብሔር እንጂ የእርሱ አይደለም፤ ሌላዉን ሳይጠቀምበት እንዲባረክለት ይኽችን 150 ብር በቅድሚያ መስጠት አለበት፤ ሲሰጥም በእግዚአብሔር ፊት እንጂ በሰዉ ፊት እንዳይሰጥ፤ ሙዳየ ምጽዋት ያስገባዉ፤
በቀድሞ ጊዜ አስራት ሲሰጥ ለአበ ነፍስ ነበር ፤ አበነፍሱም የተሰጠዉን ከሦስት ይከፍለዋል 150 ብሩን 50 ብር ለቤተክርስቲያን መባዕ፡ 50 ብር ለነዳያን ፡ 50 ብር ለራሱ ይወስዳል ፤ ይኽ በአሁኑ ዘመን ስለማይሠራ ካህናቶቻችን በገቢ የደከሙ በመሆናቸዉ የነፍስ ልጆቻቸዉ ተጧሪዎች ሆነዋል፤ የጥንቱ የአባቶቻችን ሥርዓት ግን ትክክለኛ ነበር፤ ይኽ አሁን ባለን ባለሃብቶች ትክክለኛ አስራት ቢሰላ እና ቢሰበሰብ ቤተክርስቲያንም ካህናትም ነዳያንም ለጋሾች እንጂ ተጧሪዎች አይሆኑም ማለት ነዉ፤
እኛ ዛሬ ይኽን ሥራ ብንጀምረዉ ፈጣሪ ረድቶን ከቀድሞዉ ዘመን የአባቶች በረከታዊ ኑሮ መሳተፍ እንችላለን ፤ የየድርሻችንን እንወጣ ፤ ከራሳችን እንጀምር፤ ከ100 ብር 10 ብር የእግዚአብሔር ነዉ ብለን ስንሰጥ ፈጣሪ በሚገርመን አመጣጥ አምጥቶ ሲያትረፈርፍልን ለማየት ምስክር ከፈለጋችሁ እኔ አለሁላችሁ!
አሥራት በመክፈል የሚገኘዉ በረከት አያምልጣችሁ ፤ ስትሰጡ ደግሞ ደረሰኝ እንዳታስቆርጡ፤ ማንም ሳያያችሁ ሙዳየ ምጽዋት ጨምሩት ፤ ወይም ደግሞ በወር የምትከፍሉትን አስራት ሰብስባችሁ ከሦስት ከፍላችሁ ከላይ በተገለጸዉ አግባብ አካፍሉ፤ መልካም አበነፍስ ካላችሁም ሲፈጽሙት እየተከታተላችሁ ሙሉዉን አስራት ስጧቸዉ፤ በራሳችሁ ሒሳብ ሳይሆን ከመቶ አስር አዉጡ ሳንቲምም ቢሆን እንዳታስቀሩ፤ ከሰጣችሁት በኋላ እግዚአብሔርን ታዘቡት ፤ (ትንቢተ ሚልክያስ 3 ፡ 10) ሙሉዉ ምዕራፍ 3 ይነበብ !
ባለ ሃብቶች እንዳትተክዙ አደራ እላችኋለሁ ፤ ግመል በመርፌ ቀዳዳ (ማቴ 19፡24) የተነገረዉ ለእናንተ ነዉና፤ ትርፋችሁን ወደ አስራት ስታሰሉ ብዙ ሆኖባችሁ እንዳትሰናከሉ በድጋሚ አደራ እላለሁ ፤ ከእናንተ አይበልጥምና ይሰዋ ፤ የሄደዉ እንደሚመጣ እመኑኝ፤ ፈጣሪ ያበርታን ፤ አሜን + + +

No comments:

Post a Comment