Tuesday, September 7, 2021

በእንተ ሃዲስ ዕዝራ

ወርሃ ጳጉሜን ወርሃ ምስጢር   ዕለተ ሠሉስ ጳጉሜን 02 2013 ዓ.ም

 ከእርሳቸዉ ጋር ስሆን ከደስታዬ ብዘት የተነሳ ሲናገሩ ሳቅ ሳቅ ይለኛል፤

አርጅቶ እንኳን በአልጋ አድርገዉ እያመጡ ያስተረጉሙት የነበረዉን ባስልዮስ ዘ ቂሳርያን ያገኘሁት ይመስለኛል፤

ሁሉ ነገራቸዉ ይገርመኛል፤

አንዴ ግን በጣም ሳልቀርባቸዉ ሳንተዋወቅ ምሽት 1፡00 አካበቢ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን ጎንደር ጉባኤ ጨርሰዉ ሲዎጡ ወደ ጉባኤ ቤቱ ጠጋ አልኩና ሰላምታ ሰጠኋቸዉ፤ ከዚያ ሁሌም የማይመለስልኝ ጥያቄ ነበር የቅዱስ ሚካኤል እና የቅዱስ ገብርኤል ጉዳይ፤

ሠለስቱ ደቂቅን የሁለቱም ድርሳን ላይ ሁለቱም እንዳዳኑ ተጠቅሷል፤ እርስዎ  ምን ይላሉ አልኳቸዉ፤

የኔታ ሊቁ ዕዝራ ትንሽ አሰቡና እንደተለመደዉ ወደ ሰማይ ቀና ብለዉ አዩ፤ ክስት ሊተ እንደ ማለት ፤

እኔ ጓጉቼ ዓይን ዓይናቸዉን አያለሁ፤ አጭር ቃል ተናገሩ ፤

ቅዱስ ሚካኤል ካለበት ቅዱስ ገብርኤል አይታጣም ፤ አንድ ክንፋቸዉ የገጠመ ነዉ አንድ ክንፍ ለሁለት ነዉ የሚጠቀሙት ሲሉኝ እጅግ ስለፈራሁ ሌላ ጥየቄየን ሳላስከትል “ ፍልጥ ዘትትዋነይ ኦ ገብረ ማርያም ንዑስ ” አንተ ትንሽ ሰዉ አቅምኽን እወቅ ብዬ ሹልክ ወደ ቤቴ……… ከዚያ በኋላ ምስጢር መርማሪ ሆንኩ እላችኋለሁ፤ እነ ጥራዝ ነጠቅ ያሳዝኑኛል፤

ብጹአዊ አባታችን አቡነ ኤልሳ በሕይወተ ስጋ ሳሉ የኔታ ሊቁ ዕዝራ ሲያስተምሩ እጅግ ስለተደሰቱ የረቀቀ ስም ሰጧቸዉ ዕዝራ ሃዲስ የሚለዉን የራሳቸዉን ስም በመገልበጥ ፤ ሃዲስ ዕዝራ አሏቸዉ አንተ ሁሌም አዲስ ነህ ለማለት ………..

ከእርሳቸዉ ጋር ለ8 ዓመታት በጉባኤ ቤቱ አስተባባሪ ኮሚቴነት የሒሳብ ሹም ሁኜ ተገልግያለሁ፤ የስጋ ነገር ሁኖ ቢሮ እየዋልን እንጂ 8 ዓመት ጉባዔ ባሔድ ኑሮ መጋቤ ብሉይ ወሃዲስ ወሊቃዉንት የሚል ስም ይለጠፍልኝ ነበር ፤ ዋናዉ ግን መብረቅ ይወልድ መብረቀ እንዲል እርሳቸዉን አስመስለዉ እንጂ እርሳቸዉን አሳክለዉ የወለዷቸዉ የሉም ፤ ግን እንጠብቃለን !

እንዲህ ዓይነት ሰዎች ሲያልፉ ነዉ የሚወደሱት፤ ሲቀሩብን ነዉ የምናዉቃቸዉ፤ እጅግ ብዙ ዉስጣዊ ፈተናዎችን አስተናግደዋል፤ ተሃድሶ መናፍቃን ከእግራቸዉ ስር ይፈላሉ፤ የቅርብ ሰዎቻቸዉ በተለያየ ሁኔታ ይዘምቱባቸዋል ነገር ግን እርሳቸዉ ሁሌም አንድ ነገር ይናገራሉ ……. የጉባዔዉ አምላክ እርሱ ባለቤቱ ያዉቃል ይላሉ፤

የንግሥ በዓላት ድምቀት ናቸዉ ፤ ሊቃዉንት ከእርሳቸዉ ፊት ሲሆኑ ምስጢርን ማራቀቅ ማንነታቸዉን ለማሳየት ይሽቀዳደማሉ፤ የመንግሥት ባለስልጣናት ታሪክ አዋቂ በመሆናቸዉ ይፈሯቸዋል፤ የጵጵስና ማዕረግ ቀርቦላቸዉ አሻፈረኝ ብለዋል ላለመቀበል ሳይሆን ብዙ ለመስራት ሲሉ፡፡

በትምህርታቸዉ በመድረካቸዉ በጉባዔያቸዉ ኢንጂነር፣ የባንክ ባለሞያ ፣ ፔዳጎጂካል ፣ የኢኮኖሚ ተንታኝ፣ ፖለቲከኛ፣ አስታራቂ ፣ የጤና ባለሞያ፣ ፈላስፋ ፣ ቲያትረኛ፣ ሃያሲ፣ ጋዜጠኛ፣ ዲፕሎማት ፣ ጠበቃ ፣ ዳኛ ፣ወታደር፣ ሁነዉ ታገኟቸዋላችሁ፤

ጥበቡን መድኃኔዓለም በግልጽ እንደሰጣቸዉ ያስታዉቃል፤ ነገር ግን እርሳቸዉ ጋሻጃግሬ አስተዋዋቂ ስለሌላቸዉ ከእነ ኣያ እገሌ እኩል አይታወቁም፤ በቤተክርስቲያኗ ቴሌቪዥን እንኳን ከብዙ ጊዜ በኋላ ነዉ ብቅ ያደረጉዋቸዉ የሚያዳርሱትን ካዳረሱ በኋላ፤ አበዛሁ መሰለኝ

አንድ ብቻ ነገር ልንገራችሁ እና ላብቃ ፡

ከእኔ ጋር ለጉባዔ መተማ ዮሐንስ ከተማ ጥር 04 ቀን 2008 ዓ.ም እየወሰድኳቸዉ የነገሩኝን ላካፋላችሁ እጅግ በጣም ስለገረመኝ፤

ደብረ ሊባኖስ ለትሩፋት ከጻድቁ በረከት ለማግኜት ሄድኩና አልባሌ ልብስ ለብሼ የሹራብ ቆብ አድርጌ ለሁለት ሳምንታት ለተጠማቂዉ ጸበል ስቀዳ ሰነበትኩ ፤ በኋላ አንዲት ሴት አወቀችኝ በምን አወቅሽኝ ስላት ሳቅ ስትል በጥርስህ አወቅኹኽ አለችኝ በኋላ መነኮሳት ተሰብስበዉ አስተምረን ብለዉኝ አስተምሬ ብዙም ሳልቆይ ወደ ጎንደር ተመለስኩ፤ እና ሰዉ ልታወቅ እወቁኝ ካለ በቀላሉ ይታወቃል እራሱን ልደብቅ ካለም እንደዚያዉ ፤ ያሉኝ ሁሌም አይረሳኝም ፤ መተማ የሆነዉን ብዙ ድንቅ ነገር አላነሳም ግን በትምህርታቸዉ ሙስሊሞች ተጠምቀዋል፡፡

በለተይ ጎንደርን የሃይማኖት ተጠያቂ በመሆኗ ፈጣሪ ያለ አንድ ሊቅ እንደማይተዋት ማረጋገጫችን ስለሆኑ መድኃኔዓለም ከክፉ ሁሉ ይጠብቅልን፤ እኔም ትንሽም ቢሆን ከእርሳቸዉ ጋር በነበረኝ ቆይታ ምስጢርን እንዳዉቅ እንድመረምር እና በዕምነቴ በሃይማኖቴ በራስ መተማመን እንዲኖረኝ ያደረገኝ ፈጣሪ ክብር ምስጋና ይድረሰዉ፤ አሜን + + +

No comments:

Post a Comment