Thursday, June 25, 2020

የመቁጠሪያ ጸሎት አደራረስ !


ሰላም ለኩልክሙ!

ግንቦት 12 ቀን 2012 ዓ.ም በበዓለ ቅዱስ ሚካኤል ( እንደ ሰዉ ያለ መልአክ)

ቤተክርስቲያናችን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እና ሃገራችን ኢትዮጵያ ካሏቸዉ እልፍ አዕላፋት መነኮሳት እና መነኮሳይት ግንባር ቀደም ሆነዉ የሚጠቀሱት ከወንዶች አቡነ ተክለሃይማኖት ሲሆኑ ከሴቶች ደግሞ ቅድስት ክርስቶስ ሠምራ ናቸዉ፤ የዛሬዉ የሁለቱም ዓመታዊ በዓል ሙሉ ታሪኩን (ዝክረ ሊቃዉንት በፌስቡክ - ዲን. ዮርዳኖስ )በሚገባ የሚዘግብልን ስለሆነ መመልከት እንችላለን ፤
 እኔ ግን ከዛሬዉ በዓል ጋር እንድንማር የፈለግሁት ሁለቱም ጻድቃን ከፈጣሪያቸዉ ጋር ከሚገናኙበት እና ጠላት ሠይጣንን ድል ከነሱበት ከመነኮሳት የማይለየዉን የመቁጠሪያን ጸሎት አደራረሱን ይሆናል፤ ባለንበት ሆነን በመቁጠሪያ መጸለይ መነኩሴ መሆን አይጠይቅም ፤ በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ስለሚያደርሱ ለመነኮሳት የተተወ አድርገን መቁጠር የለብንም፤ የመቁጠሪያ ጸሎት ለሚያዘወትረዉ ብዙ ኃይልን ያደርጋል ስለሆነም ያለንን ጊዜ አመቻችተን እንድንጸልይ ፈጣሪ እንዲረዳን እየተመኘሁ አደራረሱን እንሆ !
መቁጠሪያ ብዛቱ 41 ወይም 64 ሆኖ ሊሰራ ይችላል 41 ቢሆን የክርስቶስን ግርፋት እያስታወስን እንድንጸልይ፤ 64 ቢሆን መላ ዘመኗን በመከራ ያሳለፈች እናታችን ድንግል ማርያምን እያሰብን እንድንጸልይ ይዘጋጃል፤ የተለመደዉን ባለ 41 መቁጠሪያዉን ከገዛን በኋላ በአባቶቻችን ማስባረካችን እንዳንረሳ ! (ባለ 64 መቁጠሪያ 41 ጊዜ ለማድረስ ስለማይመቸን እንጂ ቢኖረን መልካም ነዉ)
በቀን ሰባት ጊዜ እንድንጸልይ መጻሕፍት ያዛሉ ፤ የግል ጸሎታችን እንደ ችሎታችን አድርገን የመቁጠሪያ ጸሎቱ ግን በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት በእያንዳንዳቸዉ 12 አቡነዘበሰማያ፤9 ጸሎተ ማርያም እንዲሁም 41 ጊዜ የሚጸለዩ የሚጸለዩ፤
41 ጊዜ እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስ
41 ጊዜ በእንተ እግዝእትነ ማርያም መሃረነ ክርስቶስ
41 ጊዜ ኪርያላይሶን
41 ጊዜ አምላኪየ
41 ጊዜ በከመ ምኅረትከ አምላክነ ወአኮ በከመ አበሳነ
41 ጊዜ ተዘከረነ እግዚኦ በዉስተ መንግስትከ  41 ኛዉን  ስንጨርስ በከመ ተዘከርኮ ለፈያታዊ ዘየማን እንዘ ሃሎከ ዲበ እፀ መስቀል ቅዱስ እንላለን
41 ጊዜ ኤሎሄ ብለን ማሳረጊያዉ ፤
ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ( እንድናመልከዉ ለፈጠረን እግዚአብሔር ምስጋን ይገባል)
ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግዝእትነ ወመድኀኒትነ ( ለእመቤታችን ምስጋና ይገባል)
ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ እፀ መድኃኒት ኃይልነ ወጸወንነ ( መጠጊያ መድኃኒት ኃይል ለሆነን ለክርስቶስ መስቀል ምስጋና ይገባል ) ብሎ በጸሎተ ሃይማኖት እና በአቡነ ዘበሰማያት ይፈጸማል ፤
ከላይ የተጠቀሰዉ የመቁጠሪያ ጸሎት ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚጸለይ ሲሆን በሰባቱ የጸሎት ጊዜያት ፤
7 ጊዜ 12 አቡነ ዘበሰማይት 84 ጊዜ ለፈጣሪያችን እናደርሳለን ማለት ነዉ
7 ጊዜ 9 ጸሎተ ማርያም(ሰላም ለኪ) 63 ጊዜ ለእመቤታችን እናደርሳለን የአንድ ጊዜዉን ሰላም ለኪ 10 ጊዜ ስናደርሰዉ በእመቤታችን እድሜ 64 ጊዜ አደረስን ማለት ነዉ፤
አንድ አንድ አባቶች በዓለም ሆኖ ስራ የሚበዛበት ሰዉ ጠዋት ቀደም ብሎ 84 አቡነዘበሰማያት እና 64  ሰላምለኪ እና በ41 ጊዜ የሚባሉትን አንድ ጊዜ አድርሶ መሄድ እንደሚችል ያሳስባሉ፤ ይኽ ሁሉ ጸሎት ተጸልዩ እግዚአብሔር ያሰብነዉን ካልፈጸመልን በልባችን ቂም በቀል ፤ ኃጢአት አለ እና ንስሐ ልንገባ ያስፈልጋል፤ በጸሎት እንድንበረታ መንፈስቅዱስ ያግዘን ፤
አምላከ ቅዱስ ሚካኤል ፤አምላከ ላሊበላ፤ አምላከ ተክለሃይማኖት፤አምላከ ክርስቶስ ሠምራ  ያሰብነዉን ይፈጽምልን ፤ መሪዎቻችንን ወደ እርቅ እንዲመጡ የቅዱስ ላሊበላን ልብ ያድልልን ፤ ሃገራችንን እና ሕዝቦቿን ወደ ቀደመዉ ክብራችን ይመልስልን፤ መንፈስ ቅዱስ ምስጢሩን ይግለጽልን፤ አሜን + + +


No comments:

Post a Comment