Thursday, June 25, 2020

ጸሎት እና አከፋፈሉ !

ግንቦት 11 ቀን 2012 ዓ.ም

ጸሎታችንን የሚያስተምረን መንፈስ ቅዱስ ነዉ፤ አፋችን ሲከፈት ቃላትን የሚመላልን ፤ ሠዉ እንዴት መጸለይ እንዳለበት በሕገ-ልቡና በልቡ ላይ ይሳልለታል ደክሞኛል ብሎ ካልተወዉ፤ አባቶቻችን ደግሞ በጸሎት መሠጠም ለረዥም ጊዜ ስለሚያቆየን ከዕለት ግብራችን ጋር በተመጣጠነ እንዴት አሳጥረን መጸለይ እንዳለብን ያስተምሩናል፤ እነሱ የተገለጠላቸዉ ጸሎት እንዲበዛላቸዉ ሌላ ምስጢር እንዲገለጽቸዉ ለእኛ ከፍለዉ ያስተምሩናል፤ ስለሆነም እኛ ከምናዉቀዉ ከፍለን ስንሰጥ ስናስተምር እንደ አባቶቻችን ሌላ ምስጢር ይሰጠናል፤ ሠዉ የተገለጠለትን ምስጢር ካላካፈለ ሌላ ምስጢር አይሰጠዉም፤ ይኽን እመኑኝ ፤ስለሆነም ለምታዉቁ ሳይሆን ለማታዉቁ የፌስቡክ ቤተሰቦቼ የመዝሙረ ዳዊትን አከፋፈል እነግራችኋለሁ፤ ለማያዉቁ ብቻ አሳዉቁ፤
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መዝሙረ ዳዊትን በሚጸልይ ሰዉ ልጄ ክርስቶስ ደስ እንደሚሰኝ ፤ ዉዳሴ ማርያምን እና ቅዳሴ ማርያምን አስተባብሮ የሚጸልየዉን አልለየዉም (ዉዳሴ ማርያም ትርጓሜ) እንዳለች ከመዝሙረ ዳዊት የሚበልጥ ጸሎት የለም ፤ ስለሆነም በዕለት ጸሎታችን የምናስቀድመዉ መዝሙረ ዳዊትን ይሆናል ( በግዕዝ ቢሆን ይመረጣል)
አንድ ሰዉ ሲጸልይ ንጽህናዉን ከጨረሰ በኋላ ቤተክርስቲያን ካልሆነ የሌሊት ልብሱን አዉልቆ መደበኛ ልብሱን ለብሶ ሻማ አብርቶ ወደምስራቅ ዞሮ በሚለብሰዉ ኩታ(ፎጣ) ታጥቆ ስዕለ አድኅኖ ፊት ቀጥ ብሎ መቆም አለበት ፤ በመጀመሪያ 7 ጊዜ ይሰግዳል 3 ለስላሴ 1 ለእመቤታችን 1ለክቡር መስቀሉ 1 ለቅዱስ ሚካኤል እና መላዕክት 1 ለቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ(ከእርሱ የሚበልጥ ስለሌለ) እና ለምድራዉያን ቅዱሳን፤
ከዚህ በኋላ አአትብ ብሎ የዘወትር ጸሎት እስከ እሰግድ ለአብ ከጸለየ በኋላ የሚችል አስርቆት ይላል( ማመልከቻ ማለት ነዉ) ማመልከቻ ሲጻፍ ቀን ወር ዓመተ ምህረት፤ የሚመለከተዉ ጉዳይ፤አድራሻ እንዳለዉ እንዲሁ ዛሬ ያደረዉ ሌሊት፤መዓልት ፤ጨረቃ፤ዓ.ዓ. ዓ.ም ወንጌላዊ ይሰላል ፤ መጻህፍትን ተመልከት!  ያልቻለ አቤቱ አምላካችን በዛሬዉ ዕለት ቀን ወር ዓ.ም ጠቅሶ የምጸልየዉን ጸሎት ተቀበልልኝ ብሎ ስብሐት ለአብ ይልና በአቡነ ዘበሰማያት ያስራል፤
በመቀጠል ወደ ዳዊቱ መዝሙር የዕለቱን በማዉጣት ይጸልያል፤
-       የሰኞ መዝሙረ ዳዊት  እንዲገባን 1፤11፤21 ማለት መዝሙር ከ 1 እስከ 10፤ ከ11 እስከ 20 ፤ ከ21 እስከ 30 ማለት ነዉ ፤
-       የማክሰኞ  31፤41፤51
-       የረቡዕ  61 እና 71
-       የሐሙስ 81፤91፤101
-       የዓርብ 111እና 121
-       የቀዳሚት 131 እና 141 ማለት እስከ መዝሙር  150 እና ጸሎት በእንተ ርዕሱ አጭሯ ጸሎት ትጸለያለች (151) እና መሐልይ ዘሰሎሞን
-       የሰንበተ ክርስቲያን (እሁድ)  ከሙሴ እስከ ስምኦን ጸሎተ ነቢያት በሙሉ
ጸሎቱን ስንጨርስ ማሰሪያዉ ( ማሳረጊያዉ ) ጸሎተ ማርያም (ሠላም ለኪ ነዉ) የብሉይ ጸሎት ስለሆነ
በመቀጠል ዉዳሴ ማርያም የዕለቱን እና አንቀጸ ብርሃን (የቻለ ሙሉዉን ያልቻለ ከፋፍሎ የሰኞ 3 ከማክሰኞ እስከ ቅዳሜ 2 2 ፤ እሁድ ሙሉዉን አንቀጸብርሃን) እና ይዌድስዋ መላዕክት ፤ ሲጨርሱ ማሰሪያዉ (ማሳረጊያዉ) ጸሎተ ሃይማኖት ነዉ የሊዋዉንት የእነ ቅዱስ ኤፍሬም ፤ቅዱስ ያሬድ ድርሰት ስለሆነ፤
በመቀጠል መልክዓ ኢየሱስ ይደገማል እንደ ሥጋወደሙ ይቆጠራልና ሲጨርሱ ፤
ስብሐት ለእግዚአብሔር ኪያነ ዘፈጠረ ከመ ናምልኮ( እንድናመልከዉ ለፈጠረን እግዚአብሔር ምስጋን ይገባል)
ስብሐት ለማርያም እመ አምላክ እግዝእትነ ወመድኀኒትነ ፤ ለእመቤታችን ምስጋና ይገባል
ስብሐት ለመስቀለ ክርስቶስ እፀ መድኃኒት ኃይልነ ወጸወንነ ( መጠጊያ መድኃኒት ኃይል ለሆነን ለክርስቶስ መስቀል ምስጋና ይገባል ) ብሎ በጸሎተ ሃይማኖት እና በአቡነ ዘበሰማያት ይፈጸማል ፤
በመጨረሻ የዘወትር መዝሙረ ዳዊት መዝሙር 90፤19፤22 ደግሞ አምላከ ዳዊት አምላከ ቅዱሳን በሠላም አዉለን ሃገራችን ሃይማኖታችን ጠብቅልን ፤ የሞቱትን ነፍስ ማርልን ፤ የታሰሩትን አስፈታልን፤ የታመሙትን ፈዉስልን ብሎ አቡነ ዘበሰማያት ደግሞ አንድ ጊዜ ሰግዶ ወደ ስራችን መሄድ እንችላለን ፤
የተወደዳችሁ ቤተሰቦቼ የቤተክርስቲያናችን አስተምህሮ በዚህ ይገደባል ማለት ሳይሆን እጅግ ሰፊ ነዉ ፤ መሠረታዊ ነገሮችን ለማንሳት እንጂ ፤ መንፈስ ቅዱስ የገለጸልንን መጸለይ እንችላለን ፤ በቅዱስ ያሬድ በዓል ምስጢርን ያናገረን አምላከ ቅዱስ ያሬድ ከሁላችን ጋር ይሁን ፤ አሜን + + +

No comments:

Post a Comment