Thursday, June 25, 2020

የመላእክት በሰባቱ ዕለታት ሹመት !


ሰዉ በፈቃደ እግዚአብሔር በአባት እና እናት ሩካቤ በተዋኅዶ ምስጢር በማኅጸን ዉኃ ሆኖ ተቋጥሮ በመንፈስ ቅዱስ ሠዓሊነት እናቱን ወይም አባቱን መስሎ ተቀርጾ (እናት ወይም አባት ካልመሰለ ችግር አለ! የሴት ልጅ ማኅጸን እንደ እርሻ መሬት ስንዴ ተዘርቶ ተልባ ስለማይበቅል እና የተሰጠዉን ማስገኘት ስለሚኖርበት) በሰፋድል ተጠቅልሎ ዘጠኝ ወር ሲቀመጥ በፈጣሪያችን ድንቅ ጥበብ ተጠብቆ ይወለዳል፤ ሲወለድ የአዳም ልጅ ስለሆነ ብቻ (እምነት ሳይጠየቅ) ሁለት መላዕክት በቀን እና በሌሊት ሊጠብቁት ይታዘዛሉ፤ ከመላዕክት ጋር ግንኙነታችን በዚህ ይጀምራል፤ በሃይማኖት እያደግን ስንሄድ እነዚህን መላዕክት ተጠቅመን በሰዉ ስለ ሌሎች ሰዎች ማወቅ እና መናገር እንችላለን፤
በሰባቱ ዕለታት ሰባቱ ሊቃነ መላዕክት ተሹመዉባቸዋል ፤ ጸሎታችንን ለማሳረግ እኛን ለመርዳት፤ከአደጋ እንዲጠብቁን ፤ ዉሃዎች አጋንንት እንዳያድሩባቸዉ ለመጠበቅ ፤ ስዕለት ልመና እንዲደርስልን ፤ ከደዌ ለመፈወስ ፤ ልቦናችን ወደ ጸሎትና ምስጢር ወደ መመርመር እንዲሄድ ፤ ጾም እንድናዘወትር ያለ ሰዓት እንድንበላ ከርስ ላይ ያለዉን ሰይጣን ለመገሰጽ፤ ከሳምንቱ አንድ አንድ ዕለታት ይዘዋል ፤ ለዚህ ማስረጃ ቤተክርስቲያናችን ቅዳሴ ከተፈጸመ በኋላ ህዝቡን ዲያቆኑ ከማሰናበቱ በፊት የሚጸለይ ወዕቀቦሙ(ጠብቃቸዉ) ጸሎት ላይ ወመልአከ ዛቲ ዕለት ቅድስት ፤በዚህች ዕለት በተሾመ መልአክ ብሎ ያሰታዉሳቸዋል ያን ጊዜ የመልአኩን ስም አስገብተን መጸለይ ነዉ፤ ይኽ ጸሎት በቀደሙ አባቶቻችን ጊዜ ሕዝቡ እንዲሰማዉ ይደረጋል የዛሬን አያድርገዉና በተለይ አዲስ አበባ፤ መላእክት በሰባቱ ዕለታት ስለተሾሙ በዕለቱ የተሾመዉን መልአክ አንስቶ አሳርግልኝ ማለት ይገባል፤
ሰኑይ (ሰኞ) ቅዱስ ሚካኤል - መልአከ ምክሩ ለልዑል ፤ ሠሉስ (ማክሰኞ) ቅዱስ ገብርኤል - አብሣሬ ትስብዕት ፤ ረቡዕ ቅዱስ ሩፋኤል - አቃቤ ኆኅት (የቤተ መቅደስ ጠባቂ) ፤ ሐሙስ ቅዱስ ራጉኤል - መጋቤ ብርሃናት ወሃብታት ብርሃናትን የሚያዝ ሃብት የሚያሰጥ፤ አርብ ቅዱስ ዑራኤል - አኃዜ ጽዋ ዘብርሃን ፤ ቀዳሚት (ቅዳሜ) ቅዱስ ሳቁኤል - ፈዋሴ ዱያን ፤ እሑድ ቅዱስ ፋኑኤል - ሰዳዴ ሰይጣናት ፤
ሰዉ መላእክትን መምሰል ይችላል፤ እንደገና ለመሰራት ፈቃደኛ ከሆነ ! አሁን ያለዉ አነዋወራችን በተለይ ለወጣቶች (20-40 ዕድሜ) በአለባበስ (የምዕራባዉያን አልባሳት መተዉ) ፤ በአመጋገብ (ኢትዮጵያ የራሷ ምስጢራዊ ምግብና መጠጦች አሏት) ፤በአነጋገር (እንደ አባቶቻችን ከመናገር ማድመጥን ማስቀደም እና አስቦ መናገር) ፤ እነዚህን የቤት ስራዎች የሰራ ሌላ ቢሰጠዉም አያቅተዉምና የመላእክት ቤተሰብ ወደ መሆን ይሸጋገራል ፤

No comments:

Post a Comment