Saturday, August 22, 2020

አልቦቱ ክርስትና ዘእንበለ ዝንቱ ፤ ከዚህ ዉጪ ክርስትና የለም !

 ሰላም ለኩልክሙ !

ነሐሴ 15 ቀን 2012 ዓ.ም

የድንግል ማርያም ስጋ እንዲነሳ እና እንዲያርግ ምክንያት የሆነበት !

አንድ ክርስቲያን ሊያዉቃቸዉ ግድ የሆኑ የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነገሮች ፤( ነገረ ክርስቶስ )!

ከቤታችን በትልቁ ጽፈን ልንሰቅለዉ የሚገባ ፤ ስንወጣ ስንገባ ልናየዉ ልናስተምረዉ የሚገባ ግዴታችን!

የሃይማኖታችን መሰረት ፤ በዚህ ዉስጥ ቅድስት ሥላሴ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም እና ቅዱሳን ያሉበት መደምደያ ነዉ!

9 ዓቢይ በዓላት

1.      ትስብዕት  -  ሰዉ የሆነበት የ40 ቀን ጽንስ ሆኖ በድንግል ማኅጸን የተገኘበት መጋቢት 29

2.     ልደት  -  በቤተልሔም በበረት የተወለደበት ሰዎች ሳይዉቁት እንስሳት እስትንፋሳቸዉን ያሞቁበት ታህሳስ 29

3.     ጥምቀት  - ዮር እና ዳኖስ ፤ ሰማይና ምድር፤ ሰዉና መላዕክት አንድ የሆኑበት ዉሃ የተቀደሰበት ክርስትና የተወለደበት ጥር 11

4.     ደብረ ታቦር - ሰዉ ብቻ አለመሆኑ የታወቀበት መለኮቱን በትንሹ ያሳየበት እንደየደረጃቸዉ ምስጢር የገለጸበት ነሐሴ 13

5.     ሆሳዕና -  የአህያን ታዛዥነትን ያወደሰበት፤ ንጉስነቱን ለሕጻናት የገለጸበት ፤ድንጋይን ያናገረበት ከትንሳኤ በፊት ያለዉ እሑድ

6.     ስቅለት  - በመስቀል ዙፋኑ የነገሰበት፤ መስቀልን በደሙ አትቶ ለመድኃኒትነት የሰጠበት፤ ሲኦልን ባዶ ያደረገበት አርብ

7.     ትንሣኤ - የሰዉን ስጋ አምላክ ያደረገበት ፤ መቃብርን ያሸነፈበት ፤ ደስታን ለዘለዓለም የሰጠበት እሑድ

8.     ዕርገት  - የሰዉ ስጋን ወደሰማይ ያወጣበት ፤ ምድር ጊዜአዊ መሆኗን ያረጋገጠበት  ከትንሳኤ በአርባኛዉ ቀን ያለች ሀሙስ

9.       ጰራቅሊጦስ- ለሰዉ ልጅ ጥበብን የሚሰጥ መንፈስቅዱስን የላከበት ፤ አንድነት ሦስትነት የተረጋገጠበት ከትንሳኤ በሃምሳኛዉ ቀን

 9 ንዑሳን በዓላት

1.      መስቀል - የወንበዴዎች መቅጫ ወደ መድኃኒትነት የተለወጠበት  መስከረም 17

2.     ስብከት  - ነቢያት ይርዳል ይወለዳል እያሉ የተነበዩበት መታሰቢያ ታህሳስ 7

3.     ብርሃን -  ክርስቶስ በብርሃን እየተመሰለ የሚነገርበት ታህሳስ 14

4.     ኖላዊ  - ክርስቶስ እዉነተኛ እረኛ መሆኑን የሚዘገብበት ታህሳስ 21

5.     ጌና -  የክርስቶስ ልደት በ4 ዓመት አንድ ጊዜ የሚከበርበት ዐማኑኤል ተብሎ ይከበራል ታህሳስ 28

6.     ግዝረት - ግዝረት ሳይፈጸምለት ተገዝሮ መገኘቱ የሚከበርበት ጥር 6

7.     ቃና ዘገሊላ - በሰርግ ቤት የመጀመሪያዉን ተዓምር ዉሃዉን ወደወይን የቀየረበት ጥር 12

8.     ልደተ ስምዖን - ስምዖን አረጋዊ ለ300 ዓመት ሳይሞት ቆይቶ ጌታን ያየበት የታቀፈበት በዓል የካቲት 8

9.     ደብረ ዘይት - የጌታችን ነገረ ምጽአት የሚነገርበት የዐቢይ ጾም አምስተኛዉ እሁድ  (እኩሌታ)

 እነዚህን በዓላት በቃል መያዝ ያስፈልጋል ፤ በዕለታቸዉ ስጋ ወደሙ መቀበል ክርስቶስን መዋሃድ የእርሱን በዓላት ከእርሱ ጋር ማክበር ያስፈልጋል፤ የካቶሊክ ሆነ የፕሮቴስታንት አማኞች እነዚህን በዓላት አለማክበር ከክርስቶስ ዉጪ ሌላ ክርስቶስ እንዳለ ያስቆጥርባችኋልና አክብሩት!

 በየዕለቱ በተለይ በዕለተ አርብ የማንረሳቸዉ ህማማቶቹን እያሰብን አቡነ ዘበሰማያት ልንጸልይ ይገባናል፤ ነፍሳችን ከፊቱ ስትቀርብ ያደረግኹልሽን ዉለታ ተናገሪ የምትባለዉ እነዚህን ከታች የተዘረዘሩትን ነዉ!

1.      ተአስሮ ድኅሪት - ወደኋላ አጥንቱ እስኪገጥም መታሰር

2.     ተቀሥፎ ዘባን - ጀርባዉን መገረፍ

3.     ተኮርዖ ርእስ - ራሱን መመታት

4.     ወሪቀ ምራቅ - ምራቅ በገጹ ላይ መትፋታቸዉ

5.     አክሊለ ሦክ - የእሾህ አክሊል

6.     ፀዊረ መስቀል - መስቀል መሸከም

7.     ተጸፍኦ መልታሕት - ጉንጭ መመታት

8.     ሰትየ ሐሞት - ሐሞት መጠጣት

9.     ቅንዋት ዘየማን እድ - የቀኝ እጅ መቸንከር

10.    ቅንዋት ዘጸጋም እድ - የግራ እጅ መቸንከር

11.     ቅንዋት ዘየማን እግር - የቀኝ እግር መቸንከር

12.    ቅንዋት ዘጸጋም እግር - የግራ እግር መቸንከር

13.    ዘእንግዳ ቀኖት - የደረት መቸንከር

ተዘከርዎ ለክርስቶስ ወሰናያቲሁ ኢትርስኡ - ክርስቶስን አስቡት ያደረገዉን መልካም ነገርም አትርሱ !

ሃገራችን በሰማይ ነዉ ፤ ደግ እንሁን ፤ በተስፋ እንኑር፤ መልካሙን ብቻ እናስብ፤ ክፉ ከአፋችን እንዳይዎጣ ምላሳችን እንቆጣጠረዉ፤ በየቀኑ ምን ያህል መልካም ነገር ተናገርኩ ብለን ራሳችንን እንጠይቀዉ፤ አምላካችን በሰማይ በደስታ እንድንኖር ያድርገን ፤ የእመቤታችን ድንግል ማርያምን ትንሳኤ ሃዋርያት እንዳዩ ሃገራችንን ትንሳኤዋን ያሳየን ፤አሜን ! ! !




No comments:

Post a Comment