Wednesday, January 13, 2021

በዓል እና ባሕል ለየቅል !

መስከረም 22 ቀን 2013 ዓ.ም

በዓል እና ባሕል ለየቅል !

ድልድዩን ሲሻገሩ የዝሆኑ ጀርባ ላይ ሁና ድልድዩን አንቀጠቀጥነዉ ያለችዉ አይጥ ትዝ ስትለኝ ፈገግ እላለሁ፤

የከንፈር እና የልብ ሁለት ኢትዮጵያዎች ያሉ ይመስለኛል፤ የልብ ኢትዮጵያችንን ይጠብቅልን !

አንድ በዓል ሲከበር ለማክበር የማይወጡ ነገር ግን ከፈጣሪ ጋር ያሉ ሰዎች በጣም ያስገርሙኛል፤ያስደስቱኛልም!

እነርሱ በዓልን የሚያከብሩት ተሰጥመዉ ዉስጠ ገብተዉ እንጂ ጎን ያለዉን ጓደኛቸዉ ምን ለበሰ፤ ምን ተናገረ፤ እንዴት አከበረ፤ የትኛዉ ሚዲያ ተገኘ፤ የትኛዉ ሹም ታደመ፤ የትኛዉ ንግግር አማረ፤ የትኛዉ ንግግር አጠረ፤ በምን ያኽል ጊዜ ተጠናቀቀ፤ የትኛዉ ተባለ የትኛዉ ሳይባል ቀረ፤ ብለዉ አይደለም፤

እነርሱ የሚተራመሰዉን ሰዉ ሳይሆን የሚያዩት ሁሌም የማይቀየሩትን ዛፎችን፤ ተራሮችን፤ መንገዶችን፤ወንዞችን፤ሰማዩን እና እንደ ሁኔታዉ የማይቀያየሩትን እኒኽን የፈጠረዉን ፈጣሪ እያዩ ያከብራሉ፤ ብዙ ጊዜ አደባባይ መዉጣት ደስ አያሰኛቸዉም፤ እዩኝ እዩኝ ባዩ ከተበተነ በኋላ የቦታዉን በረከት ለማግኘት ከቦታዉ ጋር ለመነጋገር ይገኛሉ፤ ቦታዉም ማን እንዴት እንዳከበረ ይዘግብላቸዋል፤

በዓል እና ባሕል ሁለቱም ለየቅል መሆናቸዉን ስለሚያዉቁ ከወርና ከሁለት ወር በፊት ምን ልለብስ ነዉ ጥያቄ አይመለከታቸዉም፤

የእነዚህ አስተዋዮች ጥበብ ሁሌም ስለሚገርመኝ እንደነሱ ባረገኝ እያልኩ እጸልያለሁ!

ወገኞቼ ! ሃገራችን ፈጣሪ አይተዋትም ብለን አምነን ሁሌም እንጸልይላታላን፤ በተለይ በአሁኑ ወቅት ጊዜአዊ መኖሪያችን መሆኗን ረስተን ለዘለዓለም እንደተሰጠችን አስበን፤ ከኛ በላይ ማንም ሊኖርባት አይችልም እያልን ጀመርነዉ ገመድ ጉተታ ትርፉ ድካም ብቻ ነዉ፤

ለዘለዓለማዊ መኖሪያችን እንደማሰብ ለዚህ እንደ መኪና ጎማ ለሚተነፍስ ዕድሜ ባለማወቃችን እንደጅብ የጎንዮሽ እየተያየን መኖሩ ዉርደት ነዉ፤ ዛፉ ወንዙ ሰማዩ መንገዱ ሁሉም ፍጥረታት እየታዘቡን እንደሆነ ማወቅ ይገባናል፤ 

አንድ ነገር ብቻ እናስተዉል፤ ሕዝብ ጠላ እግዚአብሔር ጠላ !!! አባቶቻችን የሚናገሩት ብሒል ያለምክንያት አየደለም፤

ሕዝብ ምን አለ ፤ ወደደዉ ወይስ ጠላዉ ፤ ከጠላዉ ልተወዉ ፤ ከወደደዉ ላድርገዉ የሚል መሪ ካለ ይኽችን የኮንትራት ጊዜአዊ ዕድሜ ደስ ብሎን እናልፋለን፤ ይኽ ካልሆነ ግን እጅ አመድ አፋሽ ሁኖ ፤ 99 በመቶ ብትሰራ በ1 በመቶ ስህተት በዜሮ እየተባዛ ድካም ከንቱ ይሆናል፤ ፈጣሪም በጠብታ ዋንጫዋ ስትሞላ ክንዱን ይዘረጋል፤ ያን ጊዜ የነበረዉ እንዳልነበር ይሆናል፤

በማስተዋል እንጓዝ፤ ከልብ እንጂ ከከንፈር አንዋደድ፤ ሃገሪቱም ፈጣሪ ለሚያኖራት እኛ አንዘዝባት፤ እኩልነት ሳይሆን መከባበር ይቅደም!

መዝሙረ ዳዊት 71 የየዕለት ጸሎታችን እንዳልተዘነጋ ይሰማኛል፤ ኃይል የእርሱ ብቻ ስለሆነ ፤ የከንፈሯን ሳይሆን የልብ ኢትዮጵያችንን ይጠብቅልን ፤የበረከት ዘመን ያድርግልን፤ አሜን + + +


No comments:

Post a Comment